የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ብር 265 ሚሊዮን የተጣራ ትርፍ ማግኘቱ ተገለጸ Duplicate 0

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 6 ወራት አፈጻጸም ብር 265 ሚሊዮን የተጣራ ትርፍ ማግኘቱ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው ድርጅቱ የ2014 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙንና የቀጣዩን ስድስት ወራት ዕቅድ የድርጅቱ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ እና አባላት፣ የድርጅቱ የበላይና መካከለኛ አመራሮችና የድርጅቱ ሠራተኞች በተገኙበት ጥር 28 እና 29 / 2014 ዓ.ም በቢሾፍቱ ባዘጋጀው የግምገማና የምክክር መድረክ ላይ ነው፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የድርጅቱ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተካ ገ/የስ እንደገለጹት ድርጅቱ ከነበረበት አሰከፊ ችግሮች ወጥቶ የሪፎርም ሥራዎችን በማከናወን ለትርፋማነት መድረሱ፤ የድርጅቱ ሠራተኞችና አመራሮች ጥምር ውጤት ሲሆን ይህንን ውጤት አጠናክሮ በመቀጠል ኢኢግልድ በቀጣይም የተሸለ ውጤት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት መስራት ይገባል፡፡

አያይዘውም በድርጅቱ የተሻለ አደረጃጀትና የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት ከተደረገው የእስካሁኑ ጥረት በተጨማሪ በቀጣይም ጊዜያት የተጀመረሩትን የሪፎርም ሥራዎች በማጠናከር ወደላቀ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የአመራሩና የሰራተኞች ተቀነቀጅቶ መስራት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ የሺመቤት ነጋሽ እንደገለጹት የድርጅቱ አመራሮችና የዲስትሪክትና የሽያጭ ቅርንጫፍ ሃላፊዎች ድርጅቱን ወደተሸለ ደረጃ ለማሻገር የተጀመሩትን የሪፎርም ስራዎች በማስቀጠል በተጠናከረ መንገድ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመግባት ከወዲሁ በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል፡፡

አያይዘውም የድርጅቱ የበላይ አመራር የአሰራር ክፍተቶችን በመሙላት ድርጅቱን ወደተሻለ ደረጃ የሚያሻግር አሰራሮን የመተግበር ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በተካሄደው በዚሁ የግምገማና የምክክር መድረክ የድርጅቱ የ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርትና የቀሪዎቹ ስድስት ወራት እቅድ በስትራቴጂክ እቅድ ዝግጅትና ግምገማ ዳይሩክቶሬት ቀርቦ በጥልቀት ግምገማና ውይይት ተካሂዶበታል፡፡

በአዮዲን ያልበለጸገ ጥሬ ጨው ለምግብነት የሚያቀርቡ አካላት ከህገወጥ ተግባራቸው እንዲታቀቡ ጥሪ ቀረበ::

በአዮዲን ያልበለጸገ ጥሬ ጨው ለምግብነት በማቅረብ የህብረተሰቡን ጤና አደጋ ላይ መጣል ህገወጥ ተግባር መሆኑንና በዚህ ህገወጥ ተግባር የተሠማሩ አካላት ከዚህ ተግባራቸው እንዲታቀቡ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት እና የንግድ ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በአዲስ አበባ ከተማ ኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል በጥሬ ጨው አቅርቦት፣ ግብዓትና ሥርጭት ላይ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ታህሳስ 21 ቀን 2014 ዓ.ም አሳሰቡ፡፡

የኢግልድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ የሺመቤት ነጋሽ በዚሁ መድረክ ላይ እንዳመላከቱት የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ለአምራች ኢንዱስትሪዎቻችን የኢንዱስትሪ ጨው በብቸኝነት እንዲያቀርብ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በተሠጠው ኃላፊነት መሠረት ወደ ሥራ ከገባ በኋላ በርካታ ችግሮችና ውጣ ውረዶችን በመጋፈጥ ኃላፊነቱን ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡

አያይዘውም በኢንዱስትሪ ጨው አቅርቦት ሒደት ምርቱ ለማን፣ መቼ እንዴት ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚቻል የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት እያንዳንዱ የቆዳ ፋብሪካ ሰብሳቢና አቅራቢ ድርጅቶች እንዲሁም ጨው ለግብዓት የሚጠቀሙ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ምርቱን በአግባቡ በሥራ ላይ ለማዋላቸው ማረጋገጫ እንዲቀርብ የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቶ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ጉዳዩ በንግድና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚ/ር እና በሌሎች ተቆጣጣሪና ክትትል በሚያካሂዱ ባለድርሻ አካላት የሚጣራ ጉዳይ ሆኖ ምንጩ ከየት እንደሆነ ያልታወቀ በአዮዲን ያልበለጸገ ጨው ለህብረተሰቡ ለምግብነት ገበያ ላይ እየቀረበ እንደሚኝ የገለጹት ወ/ሮ የሺመቤት ይህ ህገወጥ ተግባር ከየትና በማን እየተከናወነ እንደሚገኝና አፋጣኝ መፍትሄ እንደሚያስፈልገውም አመልክተዋል፡፡

በተጨማሪ የኢኢግልድን ምስል በማጠልሸት የራሳቸውን የምግብ ጨው አምራች ድርጅቶቻቸውን ሀብት ለማካበትና የተሸለ ምሰል ለመገንባትና በተቃራኒው ደግሞ የኢንዱስትሪ ጨው በብቸኝነት ለአምራች ኢንዱስትሪዎችና ሌሎችም ተጓዳኝ ማህበራት የሚያቀርበውን ኢኢግልድን ከኢንዱስትሪ ጨው ንግድ ለማስወጣት የሚደረግ የሴራ አካል እንደሆነ በውይይቱ ላይ የተነሳ ሲሆን ኢኢግልድ በዚህ ዓይነት ሕገወጥ ተግባር ውስጥ ስሙ ሊነሳ እንደማይገባ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

በማጠቃለያም እየተካሔደ ያለው በአዮዲን ያልበለጸገ የምግብ ጨው ሥርጭት የህብረተሰቡን ጤና በእጅጉ የሚጐዳ በመሆኑ በዚህ ተግባር የተሠማሩ ሕገወጥ አካላትን በሚመለከታቸው ተቆጣጣሪ የመንግሥት ተቋማት ክትትል በማድረግ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝና በቀጣይም ክትትሉ፣ ቁጥጥሩና የሚወሰደውም ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በምክክር መድረኩ ላይ ተሳታፊ የነበሩ የንግድና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር፣ የሚመለከታቸው ባለድርሻና ተቆጣጣሪ መ/ቤቶች ኃላፊዎች አጽንኦት በመስጠት አሳስበዋል፡፡

በዚሁ የምክክር መድረክ ላይ በኢንዱስትሪ ጨው አቅርቦት፣ ስርጭትና ግብይት ዙሪያ አቶ ዮናታን ሲሳይ በኢኢግልድ የግብዓት ግዢና ሽያጭ ዘርፍ የቃሊቲ ዲስትሪክት ሃላፊ አጭር ጥናታዊ ጽሁፍ ለተካሄደው ውይይት በመነሻነት አቅርበዋል፡፡

በውይይት መድረኩ በቆዳ ዘርፍ የተሰማሩ አምራቾች፣ የቆዳ ኢንስቲትዩት፣ የንግድ ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የምግብና መድሃኒት አስተዳደር ባለሥልጣንና ሌሎችም ጉዳዩ በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል፡፡