ተልዕኮ
  • በብቁ የሰው ሀይልና ቴክኖሎጂ በተደገፈ የአሰራር ስርዓት በመታገዝ እና ጠንካራ የአቅርቦትና ግብይት ሰንሰለት በመፍጠር ጥራታቸውን የጠበቁ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በማልማት በማቅረብ እና የተመረጡ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ በማድረግ የሀገሪቱ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ማድረግና ገበያ ማረጋጋት ነው፡፡
ራዕይ
  • በ2022 በአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ግብዓትና ውጤት ግብይት ተመራጭ የቢዝነስ አጋር ሆኖ መገኘት
እሴቶች
  • ደንበኛ ተኮር
  • ቅደሚያ ለጥራት
  • ተጠያቂነት
  • ታማኝነት
  • የቡድን ስራ
  • ምርታማነት
ተግባርና ኃላፊነቶች
  • የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን አቅርቦት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ድርጅቶችን መገንባት፤ ማስተዳደር እንዲሁም አስፈላጊ ሲሆን ማስተላለፍ፤
  • በአገር ውስጥና በውጭ አገር የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በማምረት ማቅረብ፤
  • የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር በመግዛት ማቅረብ፤
  • ከአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ፍጆታ በላይ የሆኑትን የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ወደ ውጭ አገር መላክ፤
  • የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት እና ጥሬ ዕቃ በማቅረብ በሥራ ላይ ከተሰማሩ ድርጅቶች ጋር በጋራ መስራት፤
  • ቀልጣፋና ውጤታማ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችል ጠንካራ የአቅርቦት ሰንሰለት ማኔጅመንት መተግበር፤
  • ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው በአገር ውስጥና በውጭ አገር ከሚገኙ የግልና የመንግስት ተቋማት ጋር ትብብር ማድረግ፤
  • በዋስትና የማስያዝና ከአገር ውስጥና ከውጭ የገንዘብ ምንጮች ጋር የብድር ውል የመደራደርና የመፈራረም፤
  • ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የሚረዱ ሌሎች ተዛማጅ የሆኑ ሥራዎችን ማከናወን፣ እና በተጨማሪ በደንቡ በአንቀፅ 11 በተሰጠው የአቅርቦት ክፍተቶችን ለሟሟላት፣ የድርጅቱን የገቢ ምንጭ ለማስፋትና ገበያን ለማረጋገት የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ለሽያጭ የማቅረብ ተግባራት ማከናወን ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት

1 የሸቀጦች ጅምላ ንግድ አስመጪ ድርጅት(ከ1928-2007)
ከተመሰረተ ከሰባት አስርት ዓመታት በላይ የስቆጠረው የሸቀጦች ጅምላ ንግድ አስመጪ ድርጅት (ጅንአድ) ቀደም ባሉት ዓመታት የተለያዩ ስያሜዎችን በመያዝ በተለያዩ የመንግስት ስርዐቶች ውስጥ የዘለቀና በተለያዩ የፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስርዓቶች ሲከተሉ በነበሩ የመንግስት መዋቅር ውስጥ ተፈትኖ ያለፈና አሁን የሚገኝበት ደረጃ ላይ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡


ጅንአድ በ1928 ዓ.ም የ    ውጭ አገር ዜግነት ባለቸው ባለሃብቶች የተቋቋመና አ ቤስና ኩባንያው በሚል ስያሜ በአገራችን ውስጥ በግል አስመጪነትና ላኪነት እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርቶችን በጅምላና በችርቻሮ በመሸጥ ስራ ላይ ተሰማርቶ ሲሰራ የነበረ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ነው፡፡


ድርጅቱ ስራውን በጀመረበት በዚሁ 1928 ዓ.ም ጣሊያን ሀገራችንን በመውረሯ ምክንያት ለተከታታይ አራት ዓመታት ስራውን አቋርጦ ቆይቷል፡፡ በ1933 ዓ.ም ወራሪው የጣሊያን ጦር በኢትዮጵያ አርበኞች ተሸንፎ ሲወጣ ድርጅቱ ስራውን እንደገና በመጀመር የህንጻ መሳሪያዎች፤ ጠቅላላ ሸቀጣሸቀጦች፤ የተዘጋጁ ምግቦች መድሃኒትና የቤት መኪናዎች ወደ ሃገር ውስጥ አስገብቶ ይሸጥ ነበር፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን ቡና ቆዳ ሌጦ የቅባት እህልና ጥራጥሬ ወደ ውጭ ሃገራት ይልክ እንደ ነበር መረጃዎችና መዛግብት ያመለክታሉ፡፡


በዚህ ሁኔታ እስከ 1967 ዓ.ም ሲሰራ የነበረው የአ.ቤስና ተባባሪዎቹ ኩባንያ በወቅቱ በሃገሪቱ በተቀጣጠለው አስተዳደራዊ ናፖለቲካዊ የለውጥ ጥያቄ ሳቢያ የማምረቻና የማከፋፈያ ድርጅቶችን ወደ ህዝብ ንብረትነት ባዛወረው አዋጅ(አዋጅቁጥር 20/1967) እንዲወረስ ተደረገ፡፡ የአ.ቤስና ተባባሪዎቹ ኩባንያና ሌሎችም መለስተኛ የግል ንግድ ድርጅቶችን ባንድ ላይ በማሰባሰብ የኢትዮጵያ የሃገር ውስጥ ማከፋፈያ ኮርፖሬሽን(ኢሀማኮ) ተመሰረተ፡፡ በወቅቱ 19 ቅርንጫፎች ብቻ የነበሩት ኢሀማኮ በአጠቃላይ  በ338  ሰራተኞች የንግድ ስራውን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በወቅቱ ኮርፖሬሽኑ ከመንግስት የተፈቀደ ብር 90 ሚሊዮን ካፒታል የተቋቋመና ብር 20 ሚሊዮን የተከፈለ ካፒታል ነበረው፡፡ የድርጅቱ ቅርንጫፎች ብዛት በሂደት አድጎ እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ ከዘጠና በላይ ደርሶ የነበረ ሲሆን በወቅቱ በአንድ ዋና ስራ አስኪያጅ በሁለት ምክትል ስራ ዋና አስኪያጆችና በአራት መምሪያዎች በአምስት አገልግሎቶችና በክፍለሃገራት በሚገኙ ስምንት ቀጣናዎች ተወቅሮ ሲሰራ የነበረ መንግስታዊ የንግድ ድርጅት ነበር፡፡ 


ለሁለተኛ ጊዜ ኢሃማኮን የመታው የለውጥ ማዕበል በ1983 ዓ.ም ሲሆን በዚሁ ዓመት በተከናወነው የመንግስት ለውጥ ሳቢያ በወቅቱ የነበረው አስተዳደር እንዲወገድ ተደርጎ አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው መንግስት ስልጣኑን ሲቆናቀጠጥ ለውጡ ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ በመሆኑ ማዕበሉ የቀድሞውን ኢሀማኮ አሰራርና አወቃቀር እንዲለወጥ አድርጎታል፡፡ ስለዚህ መንግስት የቀድሞውን ኢሀማኮ እና ኢትሜክስ የተባለ ድርጅት በማዋሃድ የሸቀጦች ጅምላ ንግድና አስመጪ ድርጅትን(ጅንአድ) በሚንስትሮች ምክር ቤት  በደንብ ቁጥር 103 ታህሳስ 1985 ዓ.ም እንዲቋቋም  አደረገ፡፡


ጅንአድ በወቅቱ ሲቋቋም አራት  አበይት አላማዎችን መሰረት አድርጎ ሲሆን ሸቀጦችን ከሃገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት መግዛትና መሸጥ መሰረታዊ ሸቀጦችን(ዘይትናስኳር) ከሃገር ውስጥና ከውጭ ሃገራት በመግዛት ከሃገር ውስጥ ገበያን ማረጋጋት ለሃገር ውስጥና  ለውጭ ሀገራት አምራቾችና አቅራቢዎች የአደራና የውክልና ሽያጭ ስራዎችን ማካሄድ እንዲሁም ሌሎች ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የሚረዱ ተዛማጅ ስራዎችን ማከናወን በዋናነት የሚጠቀሱ ዓላማዎች ናቸው፡፡ ድርጅቱ ሲቋቋም ከመንግስት የተፈቀደ ብር 90 ሚሊዮን የተከፈለ ደግሞ ብር 50 ሚሊዮን ካፒታል ነበረው፡፡ በወቅቱ ስራውን በአግባቡ ለመስፈጸም ይችል ዘንድ በአንድ ስራ አስኪያጅ በአምስት መምሪያዎችና በአምስት አገልግሎቶች ተወቅሮ ይሰራ ነበር፡፡ ድርጅቱ በዚህ አደረጃጀት ለ20 ዓመታት ሲሰራ ከቆየ በኋላ የተሸለ ዘመናዊ የአሰራር ስርዓት መዘርጋቱ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ከሃምሌ  2005 ዓ.ም ጀምሮ በአሁኑ ወቅት እየሰራበት የሚገኘውን መሰረታዊ የስራ ሂደት ለውጥ ተግባራዊ አድርጓል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአደረጃጀት ለውጥ በማካሄድ ቀደም ሲል የነበረውን ያሰራር ሂደት በማሻሻል በዘመናው የአሰራር ዘዴ ለመተካት ከመሰራቱም ባሻገር የሰው ሃይሉን በሰለጠኑ ባለሙያዎች የማደራጀት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡


የጅንአድ የ77 ዓመት ሁኔታ ሲገመገም በሦስት የተለያዩ የማህበራዊና ፖለቲካዊ የመንግስት አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ያለፈ እንደመሆኑ ከንጉሳዊው የመንግስት ስርዓት ውጪ በወታደራዊውም ሆነ በአሁኑ ስርዓት በተመጣጣኝ ዋጋ ሸቀጦችን ለህብረተሰቡ በማቅረብ ገበያውን የማረጋጋት ስራዎችን ማከናወንን ዋና ዓላማው አድርጎ እየሰራ የሚገኝ የመንግስት የልማት ድርጅት ነው፡፡ በዚህ አጭር መጣጥፍ የጅንአድን የረዥም አመታት ጉዞ ማቅረብ አስቸጋሪ ቢሆንም ቢያንስ ባለፉት አምስት ዓመታት የተከናወኑ ዓበይት ተግባራትን  መመልከቱ ድርጅቱ በመንግስት የተሰጠውን ገበያ የማረጋጋትና የህብረተሰቡን የሸቀጥ ፍላጎት የሟሟላት ሃለፊነት ምንያህል እየተወጣ እንደሆነ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡


በዚህ መጣጥፍ አብዛኛው ትኩረት በድርጅቱ የግዢ የሽያጭ የሰው ሃይልና የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ትኩረት የተደረገ ሲሆን ዓላማውም በእነዚህ ተግባራት ላይ በማተኮር ድርጅቱን አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም ለማሳየትና በመንግስት የተሰጠውን ሃለፊነት  በአግባቡ ለመወጣት እየተደረገ የሚገኘውን ጥረት ማመላከት ነው፡፡
ጅንአድ ከሸቀጦች ጅምላ ንግድ ጋር የተቆራ ኘስራዎችን የሚያከናውን የንግድ ድርጅት እንደመሆኑ የድርጅቱ ዓቢይ አንቅስቃሴ ከጅምላ ግዢና ሽያጭ ጋር የተያያዘ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ግዢን በተመለከተ የድርጅቱን የአምስት ዓመት እንቅስቃሴ ሲቃኝ በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ያለፈ ቢሆንም በየዓመቱ ከፍተኛ ዕድገት እንዳሳየ የግዢ አፈጻጸሙ ያመለክታል፡፡ ለአብነትም በ2002 በጀት ዓመት ከሃገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት የተከናወነው ግዢ ብር 1.76 ቢሊዮን ሲሆን በወቅቱም ግዢ የተከናወነባቸው ሸቀጦች የምግብ ሸቀጦችን ጨምሮ ወረቀት የጽህፈት መሳሪያዎች የምግብ ሸቀጦች የህንጻ መሳሪያዎች ጎማ ሸራ መለዋወጫ ጨርቃጨርቅና የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያዎች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በተመሳሳ ይመልኩ በ2006 በጀት ዓመት የተከናወነው የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ግዢ ከፍተኛ ዕድገት በማሳየት ወደ ብር 11.5 ቢሊዮን ከፍ ያለ ሲሆን በዚሁ በጀት ዓመት የምግብ ሸቀጦች(የምግብዘይትስኳርፓስታመካሮኒ…) ጠቅላላ ሸቀጦች የህንጻ መሳሪያዎች ጎማና ፕላሰቲክ ጨርቃጨርቅ የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያና የጉሙሩክ ሸቀጦች ግዢ ተከናውኗል፡፡ ይህ የግዢ መጠን ከ2002 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በአምስት ዓመት ውስጥ ዕድገት ታይቶበታል፡፡ የድርጅቱም እንቅስቀሴ በየዓመቱ እያደገ ከመምጣቱም ባሻገር የህብረተሰቡን መሠረታዊ ሸቀጦች ፍለጎት መነሻ በማድረግ በገበያው ላይ የሚታየውን የዋጋ ማሻቀብ በመቆጣጠር ገበያውን የማረጋጋት ስራ የተሰራ ለመሆኑ አቅጣጫ አመላካች ነው፡፡


ከዚህም በተጨማሪ ድርጅቱ የገዛቸውን መሰረታዊና መሰረታዊ ያልሆኑ ሸቀጦች በአገሪቱ በሚገኙት 83 የሽያጭ ቅርንጫፎችና መጋዘኖች በማሰራጨት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸጡ የሚያደርግ ሲሆን በተለይም መሠረታዊ ሸቀጦችን(ስኳርና ፓልም የምግብ ዘይት) በንግድ ሚኒስቴርና በሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት በኩል እንዲሰራጭ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ከሽያጭ ጋር በተያያዘ የድርጅቱ ዓመታዊ እንቅስቃሴ ሲቃኝ ከፍተኛ ለውጥ ተመዝግቧል፡፡ በ2002 በጀት ዓመት የተከናወነው የሽያጭ መጠን በገንዘብ 1.77 ቢለዮን ብርአካባቢ ሲሆን በአራት ዓመት ውስጥ(በ2006 በጀት ዓመት) ይኸው የሽያጭ መጠን 11.63  ቢሊዮን ከፍ ብሏል፡፡ ይህ ዕድገት ሚያመለክተው ድርጅቱ በመንግስት የተሰጠውን የህብረተሰቡን መሠረታዊ ፍላጎት መሰረት በማድረግ የሸቀጦችን ገበያ የማረጋጋት ሥራ ውጤታማ ደረጃ ላይ ለማድረስ ተግቶ እየሰራ እንደሚገኝ ያመላክታል፡፡ በተለይ ያለምንም ትርፍ እየገዛ የሚያሰራጫቸው መሰረታዊ ሸቀጦች(ስኳርናፓልም የምግብ ዘይት) ህብረተሰቡን በከፍተኛ ሁኔታ ጠቅሟል፡፡ ጅንአድ በአጠቃላይ በየወሩ 25000 ሜትሪክቶን ፓልም የምግብ ዘይት ወደ ሃገር ውስጥ በማስገባት ለህብረተሰቡ ሲያሰራጭ የነበረ ሲሆን ከሀምሌ 2007 ዓ ም ወዲህ መንግስት የምግብ ዘይት ግዢ፤ሽያጭና ስርጭት በግል ድርጅቶች እንዲከናወን በወሰነው መሰረት ድርጅታችን በመሰረታዊ ሸቀጥነት የሚታወቀውን ከፓልም ዘይት ንግድ ውስጥ ወጥቷል፡፡ ስኳርን በተመለከተ በየወሩ 396,000 ኩንታል ስኳር ከሃገር ውስጥ ፋብሪካዎች በመግዛት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲደርስ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡


2 ከታህሳስ 2007 ዓ.ም ወዲህ 
ድርጅቱ ከታህሳስ 2007 ዓ.ም ወዲህ በመንግስት ቀድሞ ከሚሰራው የጅምላ የመሰረታዊ ሸቀጦች ግዢና ሽያጭ የንግድ ስራ በሄደት እንዲወጣና መንግስት አቅዶ እየተገበረው ለሚገኘው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን አቅድ ስኬታማነት ለኢንዱስትሪዎቻችን ግብዓት በማቅረብ ተሳታፊ እንዲሆን በማደራጀት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት የሚከተሉት ራዕይ፤ ተልዕኮና እሴቶች እንዲኖረው  ተደርጎ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት  በሚል ስያሜ ከታህሳስ 2007 ዓ.ም ጀምሮ በመደራጀት ወደ ስራ ተገብቷል፡፡