ኢግልድ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ አምራች ኢንዱስትሪዎችን እየደገፈ እንደሚገኝ አስታወቀ

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት (ኢግልድ) የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የግብዓት ፍላጎት ክፍተቶች ለመሙላት ብር ሁለት ቢሊዮን መመደቡን አስታወቀ፡፡

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጸሚ አቶ አስፋወሰን አለነ ኢግልድ አምራች ኢንዱስትሪዎቻችን በዓለም ዓቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ያሉባቸውን የግብዓት ማነቆ ክፍተቶችን መፍታት ከተሰጡት ተልዕኮዎች አንዱ እንደሆነ በመግለጽ ድርጅቱ ባደራጃቸው መጋዘኖቹ የተዳመጠ ጥጥ ክምችት እንዳለውና በአሁኑ ወቅት በማንኛውም ጊዜ ከጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ሊቀርቡ የሚችሉ የተዳመጠ ጥጥ ፍለጎት በአግባቡ ማስተናገድ እንደሚቻል ተብራርቷል፡፡

በያዝነውም በጀት ዓመት ብር 200 ቢሊዮን የሚገመት ግብዓት ለአምራች ኢንዱስትሪዎቻችን ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተብራርቷል፡፡

በ2010 በጀት ዓመት ለጨርቃ ጨርቅ  ኢንዱስትሪዎች ከብር 387 ሚሊዮን በላይ ፤ ለኬሚካልና ለቆዳ ኢንዱስትሪዎች ከብር 1 ቢሊዮን በላይ፤ ለአግሮ ፕሮሰሲንግ ብር ከ153 ሚሊዮን በላይ ለኢንዱስትሪ ጨው ከብር 345  ሚሊዮን በላይ በጀት ተይዞ አምራች ኢንዱስትሪዎችን የመደገፍ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የዋና ስራ አስፈጻሚው መግለጫ አመልክቷል፡፡

ድርጅቱ በያዝነው በጀት ዓመት ከሐምሌ ወር 2009 ጀምሮ እስከ ጥቅምት 2010 ባሉት አራት ወራት ከብር 439 ሚሊዮን በላይ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችና ውጤቶች ግዢ ያከናወነ ሲሆን በኢንዱስትሪ ግብዓቶች ዘርፍ የተዳመጠ ጥጥ፤ ቆዳና ሌጦ፤ የአግሮ ፕሮሰሲንግና የኢንዱስትሪ ጨው ግዢ በመፈጸም በዘርፎቹ የሚታዩን የግብዓት አቅርቦት ክፍተቶች ለመሙላት ከፍተኛ ጥረት መደረጉ ታውቋል፡፡

ድርጅቱ ከአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እስከ ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ድጋፍ እደረገ የሚገኝ ሲሆን በእስካሁኑ እንቅስቃሴው 12 የጨርቃጨርቅና 9 የቆዳ ኢንዱስትሪዎችን እንደየዘርፋቸው በግብዓት አቅርቦት ተጠቃሚ የማድረግ ስራዎች ተከናውኗል፡፡

Latest News