ኢግልድ ባለፉት አራት ወራት ከብር 674 ሚሊዮን በላይ የሚያወጣ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችና ውጤቶች አቀረበ

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት በ2010 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አራት ወራት ብር 674 ሚሊዮን በላይ የሚገመት የኢንዱስትሪ ግብዓቶችና ውጤቶች በማቅረብ በመንግስት የተሠጠውን ተልዕኮ ለማሳካት እየሠራ እንደሚገኝ የድርጅቱ ወርሃዊ ሪፖርት አመለከተ፡፡

ድርጅቱ በያዝነው በጀት ዓመት ከሐምሌ ወር 2009 ጀምሮ እስከ ጥቅምት 2010 ባሉት አራት ወራት ከብር 439 ሚሊዮን በላይ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችና ውጤቶች ግዢ ያከናወነ ሲሆን በኢንዱስትሪ ግብዓቶች ዘርፍ የአገር ውስጥና የውጭ አገር የተዳመጠ ጥጥ፤ ቆዳና ሌጦ፤ የአግሮ ፕሮሰሲንግና የኢንዱስትሪ ጨው ግዢ በመፈጸም በዘርፎቹ የሚታዩን የግብዓት አቅርቦት ክፍተቶች ለመሙላት ከፍተኛ ጥረት መደረጉ ታውቋል፡፡ከዚህም በተጨማሪ በኬሚካልና ብረታብረት ዘርፍ የግብዓቶችን አቅርቦት ለማከናወን ይቻል ዘንድ በዘርፉ ከሚሰሩ የኬሚካልና ብረታብረት ኢንስቲትዩቶች ጋር በቅንጅት ለመስራት የሚያስችሉ የአሰራር ስልቶችን ለማዘጋጀት እየተሰራ እንደሚገኝ ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

ድርጅቱ እነዚህን ዓበይት ተግባራት በተሳለጠ መልኩ ለማከናወን እንዲያስችለው የአመራሮችንና የፈጻሚዎችን የማስፈጸም አቅም ማሳደግ ተገቢ እንደሆነ በመገንዘብ በስልጠና፤ በመልካም አስተዳደርና ጸረ ኪራይ ሰብሳቢነት፤ በውጤት ተኮር ያሰራር ስርዓትና በከይዘን ትግበራ ላይ ትኩረት ሠጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡

በቀሪዎቹ ስምንት ወራትም ለማከናወን የታቀዱትን ተግባራት ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ የወደፊት የትኩረት አቅጣጫዎች የተቀመጡ ሲሆን ትኩረት በሚያስፈልጋቸው በቆዳ፤ በጨርቃጨርቅ በአግሮፕሮሰሲንግና ብረታብረት ግብዓት አቅርቦት እንዲሁም በገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶች ላይ ከፕሮጀክት ሃሳብ ማመንጨት እስከ አወጭነት ጥናት ድረስ የልማት ዘርፍ ስር የሚገኙ የስራ ክፍሎች ትኩረት ሠጥተው እንዲሰሩ ታቅዷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የፕሮጀክት ጥናት ከአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ጋራ የጋራ ዕቅድ በመንደፍ ወቅታዊ የግብዓት አቅርቦት እንዲኖር ማድረግ፤የድርጅቱን የግብዓት አቅርቦት ዕቅድ ከሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከተያዙ ግቦች አኳያ መቃኘት እንደሚገባና ከገበያ ጥናትና ማስፋፊያ ስራዎች ጋር በተያያዘ የወቅቱን አቅርቦትና ፍላጎት እንዲሁም የወደፊቱን ትንበያ ያካተተ እንዲሆን ማድረግና የደንበኞችን እርካታ ማሳደግ የትኩረት አቅጣጫ ተደርገው ተወስደዋል፡፡        

Latest News