የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ብር 265 ሚሊዮን የተጣራ ትርፍ ማግኘቱ ተገለጸ

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 6 ወራት አፈጻጸም ብር 265 ሚሊዮን የተጣራ ትርፍ ማግኘቱ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው ድርጅቱ የ2014 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙንና የቀጣዩን ስድስት ወራት ዕቅድ የድርጅቱ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ እና አባላት፣ የድርጅቱ የበላይና መካከለኛ አመራሮችና የድርጅቱ ሠራተኞች በተገኙበት ጥር 28 እና 29 / 2014 ዓ.ም በቢሾፍቱ ባዘጋጀው የግምገማና የምክክር መድረክ ላይ ነው፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የድርጅቱ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተካ ገ/የስ እንደገለጹት ድርጅቱ ከነበረበት አሰከፊ ችግሮች ወጥቶ የሪፎርም ሥራዎችን በማከናወን ለትርፋማነት መድረሱ፤ የድርጅቱ ሠራተኞችና አመራሮች ጥምር ውጤት ሲሆን ይህንን ውጤት አጠናክሮ በመቀጠል ኢኢግልድ በቀጣይም የተሸለ ውጤት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት መስራት ይገባል፡፡

አያይዘውም በድርጅቱ የተሻለ አደረጃጀትና የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት ከተደረገው የእስካሁኑ ጥረት በተጨማሪ በቀጣይም ጊዜያት የተጀመረሩትን የሪፎርም ሥራዎች በማጠናከር ወደላቀ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የአመራሩና የሰራተኞች ተቀነቀጅቶ መስራት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ የሺመቤት ነጋሽ እንደገለጹት የድርጅቱ አመራሮችና የዲስትሪክትና የሽያጭ ቅርንጫፍ ሃላፊዎች ድርጅቱን ወደተሸለ ደረጃ ለማሻገር የተጀመሩትን የሪፎርም ስራዎች በማስቀጠል በተጠናከረ መንገድ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመግባት ከወዲሁ በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል፡፡

አያይዘውም የድርጅቱ የበላይ አመራር የአሰራር ክፍተቶችን በመሙላት ድርጅቱን ወደተሻለ ደረጃ የሚያሻግር አሰራሮን የመተግበር ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በተካሄደው በዚሁ የግምገማና የምክክር መድረክ የድርጅቱ የ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርትና የቀሪዎቹ ስድስት ወራት እቅድ በስትራቴጂክ እቅድ ዝግጅትና ግምገማ ዳይሩክቶሬት ቀርቦ በጥልቀት ግምገማና ውይይት ተካሂዶበታል፡፡